በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፤ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሰራፂ ብለን፤ ምንም ለአጠይቆተ አካላት በስም፣ በአካል፣ በግብር ሶስት ብንልም በባህርይ፣ በአገዛዝ፣ በስልጣን፣ በመለኮት ይህን በመሰለው ሁሉ አንድ አምላክ ብለን አምነን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ሐዲስ ሐዋርያ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ የኣባታችን ተክለሃይማኖትን ታሪክ በአጭሩ እንፅፋለን፡፡
አባታችን ተክለሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ድላልሽ ወይም ዘረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ክፍል ከአባታቸው ከጸጋዘአብ ከእናታቸው ከእግዚእኃረያ ታህሣስ 24 ቀን በ1197ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍስሐጽዮን ብለው ኣወጡ ላቸው፡፡ መዝ-111፡1-2. በዚሁ ዓመት በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ታህሣስ 26 እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው በተአምራት “አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐ ዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ትርጓሜውም “አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ ኣንዱ ወልድም ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስም ቅዱስ ነው» ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል፡፡ ህፃን ሆኖ ማመስገን በዳዊት ቃል እንደተናገረው “ከህፃናት እና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፤ ስለጠላትህ ጠላትህን እና ቂመኛን ለማጥፋት መዝ 8:2 ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ቃል የሚተረጉምልን ነው፡፡ ካህኑ ኣባታቸው ጸጋዘአብ ግብረ ድቁናን፤ ስርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ 015 ዓመት እድሜያቸው ቄርሎስ ከተባሉት ግብጻዊ ጳጳስ ዲቁናን በ1212ዓ.ም. ተቀበሉ፡ ፡ 1ኛጢሞ 3፡10፤ ዕድሜያቸው 22 ዓመት ሲሆን 01219 ዓ.ም. ከላይ ከተገለጹት ሊቀ ጳጳስ የቅስና ማዕረግ ተቀበሉ፡፡
በዚሁ ዕድሜያቸው እንዳሉ ከጓደኞቻቸው ጋር አደን ለማደን ሔደው ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ከዚህ በፊት በደማስቆ ቅዱስ ጳውሎስን ለሐዋሪያነት እንደመረጠው እሳቸውንም ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ እንዲሆኑ መርጦ ከአውሬ ኣዳኝነት ሰውን በትምህርተ ወንጌል እያዳኑ ለመንግስተ ሰማያት እንዲያበቁ ጠራቸው:: የሐዋርያነት ስማቸውንም ተክለሃይማኖት ብሎ ሰየመው:: ተክለሃይማኖት ማለት ተክለ ኣብ፤ ተክለ ወልድ፤ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡ ከዚ ያን ጊዜ ጀምሮ ተክለሃይማኖት ተብለው መጠራት ጀመሩ፡፡ ማቴ4:18-22 ሐዋ 9፡8-19፡፡ ኣባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖት ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለነዳያን አከፋፍለው ሁሉን ትተው ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ለማስተማር በምናኔና በሐዋርያነት ተልእኮ ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ በመሆን የማስተማር ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ ሉቃ10፡3 2ኛ ቆሮ 6፡1-2 ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከ1219ዓ.ም. እስከ 1222 ዓ.ም. ድረስ በተከታታይ ወንጌልን አስተማሩ፡፡ ቀጥለውም ዘጠኝ ወር በይፋት አገልግሎታቸውን ፈጽመዋል፡፡
ሮሜ 12:7-8;; ከ1222 ዓ.ም. እስከ 1234 ዓ.ም. ዳሞት በተባለ ስፍራ በወላይታ አገር ለአስራ ሁለት ዓመታት ሕዝቡን ከአምልኮ ጣኦት ወደ ኣምልኮተ እግዚኣብሔር፤ ከገቢረ ኃጢኣት ወደ ገቢረ ጽድቅ በትምህርት እና በተአምራት መልሰዋል፡ ቤተክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ በዚያም ወቅት በወላይታ ዳሞት ዲያብሎስ በዛፍ ላይ ኣድሮ አምላክ ነኝ እያለ ለረዥም ዘመናት ሕዝብን በማሳሳት ይጠቀምበት የነጠ በረችውን ዛፍ በተአምራት ከሥሩ ነቅለው ወደ እርሳቸው እንድትመጣ አዘው ድንቅ ነገርን አሳይተዋል፡፡ ጌታ በወንጌል የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ሾላ ተነቅለህ ወደ ባህር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችኋል፡፡ ሉቃ17፡6 ያለውን አምላካዊ ቃል በተግባር ኣስመስክረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ወደ አማራ ሳይንት ወሎ በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ከኣባ ጸሎተ ሚካኤል ገዳም ተቀብለው በገዳሙ ከ 1234 እስከ 1244 ዓ.ም. ለዐስር አመታት የረድእነት ሥራ በመስራት እና ገቢረ ተአምራትን በማሳየት ጌታ በቅዱስ ወንጌል “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም ማንም ሲተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ማቴ 20:26-28 ያለውን መለኮታዊ ትእዛዝ በተግባር አሳይተዋል፡፡
ከ1244 እስከ 1254 ዓ.ም. ኣባ ኢየሱስ ሞዓ ወደሚገኙበት ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሐይቁን በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት በመርገጥ፤ ወደ ደሴቲቱ በመግባት የምንኩስና ተግባራ ቸውን በመቀጠል በግብረ ሐ ዋርያት በወንጌል የተነገረውን የአገልግሎት ትሩፋት ከፍጻሜ አድርሰዋል፡፡ በአባ ኢየሱስ ሞዓ እጅም የምንኩስናን ቀሚስ የንጽህናን ምልክት ተቀብለዋል፡፡ የሐዋ 20:33-35 ዮሐ 13፡15-17 ማቴ 14፡28-29 ከ1254 እስከ 1266 ዓ.ም. ለአስራ ሁለት ዓመታት አቡነ አረጋዊ ወደ አቀኑት ገዳም በትግራይ ክፍለ ሃገር ወደሚገኘው ደብረ ዳሞ ገዳም በመግባት በጊዜው ከነበሩት አበምኔት ከአባ ዮሐኒ የምንኩስና ቆብና ኣስኬማ ተቀብለው በገድል እና በትሩፋት መንፈሳዊ ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ፡፡ ከደብረ ዳሞ ገዳም ተነሥተው ወደ ሌላ ስፍራ ለመሔድ ሲነሱ ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት አበምኔቱና መነኮሳቱ ሊ ሸኙአቸው አርባ ክንድ ባለው ገመድ ለመውረድ እንደጀመሩ ገመዱ ከካስማው ሥር በመቆረጡ እንዳይወድቁ በተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች እየበረሩ፣ ክንፎቻቸውን እያማቱ ሦስት ምዕራፍ ያህል በርረዋል፡፡
ከዚያም ወደ ገዳመ ዋሊ ገብተዋል፡፡ በዚህም ኢሳይያስ በትንቢቱ ኢሳ 40 29-31 እግዚ ኣብሔርን በመተማመን የሚጠብቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፡፡ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፡፡» ያለው ቃል በጻድቁ ተክለሃይማኖት ሕይወት ሊተረጎም ችሏል፡፡ ከ1 266 እስከ 1267 ዓ.ም. ኣንድ ዓመት ሙሉ የትግራይ ገዳማትን በመጎብኘት ኢየሩሳሌም እና ግብፅ ያሉትን ገዳማት እና ቅዱሳን መካናትን በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡ በዚሁ ዘመን ዳዳ በተባለ ስፍራ ቁመቱ 75 ክንድ የሆነ ዘንዶ ይመለክ ነበር እና በእግዚአብሔር ቸርነት በጸሎት ኃይል ገድለውታል፡፡ በዚያም ስፍራ በዐርባእቱ እንስሳት በኪሩቤል እና በሱራፌል/ ስም ቤተክርስቲያን ኣሳንጸው ታቦት አስገብተዋል፡፡ ከሴቶችና ልጆች ሌላ ሦስት ሺህ ወንዶችን አጥምቀው ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሐር መልሰዋል፡፡ በዚህም ተግባራ ቸው መድኃኒታችን “እነሆ እባብና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ የሚጎዳችሁ ምንም የለም” ሉቃ 10፡19 ያለው ቃል ተፈጽሞላቸዋል፡፡ መዝ 90፡13-14 ከ1267 እስከ 1289 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት ስምንት ጦሮችን ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ፣ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ አስተክለው እጆቻቸውን በትምህርተ መስቀል አምሳል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም እና ሞት ነገረ መስቀሉን በማሰብ በተመስጦ ሌት እና ቀን ያለማቋረጥ በጾም እና በጸሎት በኣርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ ከመቆም ብዛት የተነሳ ጥር 24 ቀን 1282 ዓ.ም. የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡
ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ሰባራ አፅም አከበረዉ በስርዓት አኑረውታል፡፡ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቷል» 1ኛ ጴጥ 4:1-2 ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረው፡፡ ክቡር ኣባታችን ከጢኣያት ርቀው መስቀል ተሸክመው ራስን በመካድ በመስዋዕትነት ሕይወት ፈጣሪያቸውን አገልግለዋል፡፡ ማቴ 24፡27 በመዓልት እና በሌሊት በትጋት እና በቁመት በተጋድሎ ብዛት አንዲት የአገዳ እግራቸው ስትሰበር ዕድሜያቸው ዘጠና ሁለት ዓመት ሆኖ ነበር፡፡ መዝ 3፡1፣ መዝ 108፡24፣ መዝ 13:1-5 ሉቃ 18:7 21፡36 ዕብ 11፡38 ከ1289 እስከ 1296 ዓ.ም. ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራ ቸው ብቻ በመቆም ያለምግብ በትህርምት ሌትም ቀንም እንቅልፍ ዓይናቸው ሳይዞር እንደ ምሰሶ ጸንተው በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድህነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውሃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ ነው፡፡ ማቴ 4:4 ሐዋ 14፡22፣ 2ኛ ቆሮ 11:26. በዚህ ጊዜም ጌታ ተገልጾ ሰባት የሕይወት አክሊ ላት ሰጥቷቸዋል፡፡ ዝክራቸውን በማዘከር፤ መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ፍጹም ዋጋ ክብር እንደሚሰጣቸው ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ያዕ 1፡12፣ ራዕይ 14 12፡13፣ 2ኛ ጢሞ 4 ፣ 6፡8 በመጨረŠም እስከ ነሐሴ 24 ቀን 1296 ዓ.ም. ለዐስር ቀናት በሕመም ቆይተው ፈጣሪያቸው የገባላቸውን ቃል ኪዳን ለመነኮሳት ደቀመዛሙርቶቻቸው ከነገሩ በኋላ በክብር ዐርፈዋል፤ መዝ 115፡6በኣካለ ነፍስ ወደሚና ፍቁት ፈጣሪያቸው ሄደዋል፡፡ ዛሬም በአጸደ ነፍስ ሆነው የገባላቸውን ቃል ኪዳን በማሰብ ስለ እኛ ስለ ኃጥአን ይቅርታን እና ምህረትን ፈጣሪያቸ ውን በመጠየቅ በማሰጠት ላይ የሚገኙ ገድለኛ አባታችን ኢትዮ ጵያዊ ሐዋርያ ናቸው፡ ፊሊ 1፡23፣ መዝ 67፡35 ጸሎታቸውና በረከታቸው፤ ረድኤ ታቸውና ምልጃቸው በመላው ሕዝበ ክርስቲያንና በቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኣገልጋዮች ሁሉ ለዘለዓለሙ አድሮ ይኑር አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በመምህር ኃይለ ሥላሴ