ሥርዓተ ቅዳሴ

ሥርዓተ ቅዳሴ ምን ማለት ነው?

ቅዳሴ ንባብም ዜማም የሚቀርብበት የፀሎት ክፍል ነው፡፡ ሁላችንም የምንሳተፍበት ቔሱም ዲያቆኑም ምእመኑም የሚሳተፉበት ነው፡፡ “ኢትቁም እራቀከ ቅድመ ነቢየ እግዚአብሔር … በእግዚአብሔር ነቢይ ፊት ራቁትህን አትቁም” ይህ ማለት በቅዳሴ ጊዜ ሰው ካለመባ፣ ካለእጅ መንሻ በእግዚአብሔር ፊት ሳይዙ መቆም እንደሌለበት ያጠይቃል፡፡ ምንም ባይኖረን እንኳን ያለንን አነሰ ብለን ሳንሳቀቅ ደግሞም ሳንንቃት ይዘን በፊቱ መቅረብ አለብን። ከቻልን እጣኑን፣ ዘቢቡን፣ ጧፉን ሌላም ሌላም ይዘን መሄድ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ካህኑ በቅዳሴው መሃል ምዕናን ስለሚያስገቡት መባ የሚፀልየው ፀሎት አለ ምዕመኑም መባን ይዞ የማይመጣ ከሆነ ይህ ፀሎት ለማን ነው? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡

ስለዚህ ቅዳሴን የምናስቀድሰው አስቀድመን ተዘጋጅተንበት መሆን አለበት፡፡ ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ጊዜ ባይኖረን ለቅዳሴ ግን ጊዜ መድበንለት ልናስቀድስ ይገባል፡፡ ቅዳሴ ለማስቀደስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ራሳችን፦
1ኛ ቆምን ለማስቀደስ
2ኛ የሚነበቡትን መጻሕፍቶች ከሕይወታችን ጋር እያዛመድን ለማዳመጥ ለመስራት
3ኛ ቅዱስ ቁርባን ለመውሰድ የዘለዓለም ሕይወትንም ለማግኝት አምኖ መምጣት አለበት

በቅዳሴው የመግቢያ ክፍል ይህንኑ በዜማ “እስመጨረሻው ቅዳሴውን ያላስቀደስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲነበቡ ቆሞ ያላዳመጠ በመጨረሻም ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበለ ከቤተክርስቲያን ኅብረት ልጅነት ይሰደድ” ይላል። ስዚህ ራሱን አዘጋጅቶ መምጣት ይገባል፡፡ 

በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ ነገሮች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ያዝዛል፦​

 

በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል። ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።

በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።

በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።

ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል። በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።

በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።

ስለ ሥርዐተ ቅዳሴ ተደጋግመዉ የሚነሱ ጥያቄዎች

፩. ቅዳሴ ሓዋርያት ፦ በበዓለ ሓዋርያት ይቀደሳል
፪. ቅዳሴ እግዚእ ፦ በቊስቋም (ኅዳር ፮ዕለት)፣ በሕንጸታ (ሰኔ ፳፩ ዕለት) ፣ በፍልሰታ ኪዳነ ምሕረት ፲፮ ዕለት ይቀደሳል ::
፫. ቅዳሴ ዘቅዱስ ዮሓንስ ወልደ ነጐድጓድ ፦ በዘመነ ስብከት፣ በበዓለ ሓዋርያት፣ በበዓለ ሰማዕታት፣ በጽጌ ፣ በፍሬ፣ በቅዳሴ ቤተክርስቲያን ፣ በኣቤል ፣ በነቢያት፣ በዮሓንስ ወልደ ነጐድጓድ ይቀደሳል።
፬. ቅዳሴ ማርያም፦ በእመቤታችን በዓል ፣  በታሕሣሥ ፳፰ ዕለት፣ የጌና፣ በመጋቢት ፳፱ ዕለት የትስብእት ፣ በጥቅምት በ፪ ዕለት በዕረፍቱ ይቀደሳል። 
፭. ቅዳሴ ዘቅዱስ ሠለስቱ ምዕት፦ በኣማኑኤል ታኅሣሥ ፳፰ ዕለት ፣ በቃና ዘገሊላ ፣ በጻድቃን፣ በብዙኃን ማርያም፣ በማኅበረ በኵር ፣ በሠለስቱ ምዕት ፣ በ፬ እንስሳ ፣ በካህናተ ሰማይ ይቀደሳል።
፮. ቅዳሴ ዘቅዱስ ኣትናቴዎስ ፦ በግንቦት በሰባት ዕለት፣ በዕረፍቱ፣ እሁድ እሁድ ይቀደሳል።
፯. ቅዳሴ ዘቅዱስ ባስልዮስ ፦ በዘወትር ወበተዝካረ ሊቃነ ጳጳሳት ወካህናት፣ ወበተዝካረ ነገሥት ፣ በጥር በ፮ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል።
፰. ቅዳሴ ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ (ዘኑሲስ) ፦  ከኒቆዲምስ ረቡዕ እስከ ሆሣዕና ይቀደሳል።
፱. ቅዳሴ ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ፦ የጥምቀት ገሃድ፣ በምሴተ ሓሙስ ፣ በክረምት ፣ በግንቦት በ ፲፯ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል።
፲. ቅዳሴ ዘቅዱስ ዮሓንስ ኣፈወርቅ ፦ በመድኃኔ ዓለም ዕለት፣ በመስቀል ፣ በቅዳሜ ስዑር፣ በግንቦት በ፲፪ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል።
፲፩. ቅዳሴ ዘቅዱስ ቄርሎስ፦ በፈጸምነ፣ በዘመነ ዕርገት፣ በተዝካረ ሙታን፣ በተዝካረ ኣብርሃም ወኢዮብ ወኤልያስ፣ በሓምሌ ፫ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል።
፲፪. ቅዳሴ ዘቅዱስ ያዕቆብ ( ዘሥሩግ ) ፦ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል፣ በሩፋኤል በኣእላፍ ፣ በነገረ ምጽኣት ፣ በሰኔ በ፳፯ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል ። 
፲፫. ቅዳሴ ዘቅዱስ ዲዮስቆሮስ፦ በልደት፣ በጥምቀት ፣ በትንሣኤ ፣ በዕርገት፣ በጰራቅሊጦስ፣ በቅድስት ሥላሴ ፣ በመስከረም ፯ በዕረፍቱ ዕለት ይቀደሳል።
፲፬. ቅዳሴ ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ (ካልዕ / ገባሬ መንክራት) ፦ በዘመነ ልደት ይቀደሳል። ይቆየን
💒 በሥርዓተ ቅዳሴ የግል ጸሎት ማድረግ ኣይገባም። የቤተክርስቲያን ታላቁ ጸሎት ቅዳሴ ነው። ሌላ ጸሎት ቢደረግ ውኃውን ጸበል ለማድረግ፣ ህመምተኛን ለመፈወስ፣ አጋንንትን ለማስወጣት፣ ምስጋናና ልመና ለማቅረብ ለመሰለው ሁሉ ነው ጸሎተ ቅዳሴ ግን ኅብስቱን ወደ ቅዱስ ሥጋው ወይኑንም ወደ ክቡር ደሙ ለመለወጥ በመሆኑ ከጸሎት ሁሉ የቅዳሴ ጸሎት ይበልጣል። ስለዚህ በዚህ ታላቅ ጸሎት የግል ጸሎት ማድረግ ኣይገባን።
 
💐💒 ኣስተውለን ከሆነ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ ከሐዲሳት መጽሓፍት ውጪ ድርሳነ መላእክት ገድለ ቅዱሳን ኣይነበብም ይህም የሆነበት ምክንያት የጸሎቱ ዓላማ ሥርዓተ ቍርባንን ለማቅረብ ስለሆነ ነው።
 
➙ በሥርዓተ ቅዳሴ የግል ጸሎት ማድረግ እንደማይገባ በሥርዓተ ቅዳሴ መጽሓፍ ኣንድምታ ምዕራፍ ፲፩ ክፍል ፲፩ ቍጥር ፵፬-፵፭ ላይ በጊዜ ጸሎት ወቅዳሴ እንዘ ይትነበብ ቃላቲሁ ለእግዚኣብሔር ይደሉ ከመይኩኑ ኣርምሞ ወተደሞ ውስቴቶሙ ዘእንበለ ሰብሖ ወቀድሶ እምጥንቶሙ እስከተፍጻሚቶሙ። / ጸሎተ ሌሊት ነው ቢሉ መላው ጸሎት ተጀምሮ እስኪፈጸም፤ ጸሎተ ቅዳሴ ነው ቢሉ ፩ዱ(ኣሓዱ) ብሎ ዕትዉ (በሰላም ወደ የቤታችሁ ግቡ) እስኪል ጸሎት እንኳ ቢሆን ጸሎት ሳይቀር ከተሠጥዎ በቀር ኣርምሞ ተደሞ ሊሆን ይገባል። ይለናል።
 
➙ ስለዚህ እንኳንስ ጸሎተ ቅዳሴው ላይ ይቅርና የሌሊት ጸሎት (ማኅሌት) ወይም በማኅበር ጸሎት ጊዜ ላይም እንኳ የግል ጸሎት ኣግባባ ኣይደለም በማለት ነው የገለጸልን ከሊቃውንቱ ጋር ማኅሌቱን ወረቡን ሰዓታቱን ኪዳኑን ኣብሮ ማድረስ መጸለይ እንጂ የግል ጸሎት ኣግባብ ኣይደለም።
 
➙ በቅዳሴ ጊዜ የግል ጸሎትን ላድርግ ማለት በቀትር የፀሓይ ብርሃን ሻማን እንደማብራት ነው። የሻማው ብርሃን በቀትር የፀሓይ ብርሃን ይዋጣል እንጂ በብርሃነ ፀሓይ ላይ ብርሃን ኣይጨምርም። በማኅበር ጸሎት የግል ጸሎት ማድረስ ከማኅበሩ ጸሎት የኔ የግል ጸሎቴ የተሻለ ነው የበለጠ ተሰሚነት ኣላው እንደማለት ይሆናልና ኣግባብ ኣይደለም። ስለዚህ ሥርዓተ ቅዳሴ የማኅበር ጸሎት ከተጠናቀቀ በኋላ የግል ጸሎት ማድረግ ይገባል።