በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ኢትዮጵያ ቅድመ ክርስትና
ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት ስለ ነበራት ሃይማኖት ሁለት ዓይነት ታሪክ አለ።
፩ኛ. የኢትዮጵያ አቅኒዎች የመምለኬ እግዚአብሔር የኖህ የልጅ ልጆች ሳባና ሰብታ ቀጥሉም የሴም ወገን ሳባውያን ስለ ነበሩ አያታቸው ኖህ ያመልከው የነበረውን አንድ እግዚአብሔርን ማምለክ አላቋረጡም ነበር። ከዚህም የተነሣ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን ሳታውቅ የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ታውቋል። ይህንም በትውፊት ያገኘችውን አምልኮተ እግዚአብሔር ጠብቃ ከ፪ሺ፭፻፵፭-፱፻፹፪ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ኖራለች።
፪ኛ. ከ፪ሺ፲፫-፱፻፹፪ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበረችው የኢትዮጵያ ንግሥት ማክዳ (ንግሥተ ሳባ) በታሪክ የሰማችውን የሰሎሞንን ጥበብ ለማየትና በዘመኑ የነበረውን የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለማስተዋወቅ የብሉይ ኪዳንንም እምነትና ትምህርት ሥርዓቱንም ከመሠረቱ ለመረዳት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ ምኒልክ የሚባል ልጅ ከሰሎሞን ፀንሳ ተመለሰች። ምኒልክም ተወልዶ ካደገ በኋላ የአባቱን አገር ኢየሩሳሌምን ጐብኝቶ ሲመለስ ጽላተ ሙሴንና ካህናተ ኦሪትን እስከ ሰሎሞን ዘመን ድረስ የተጻፉትን በርካታ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይዞ መጥቶአል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአይሁድ እምነት (ተይህዶ) ከትምህርቱ፣ ከሥርዓተ አምልኮቱና ከመዐርገ ክህነቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶአል። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ወደ ጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋ ግእዝ መተርጐም የተጀመሩት ያንጊዜ ነበር።
ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳን እምነትን መቀበልዋን የሚያስረዳ ታሪክ ብቻ አይደለም። እስከ ዛሬ ድረስ በሕዝቡ ዘንድ የሚታዩት የተለያዩ ባህሎችና ትውፊቶችም ዋና ማስረጃዎች ናቸው።
ለምሳሌ:- ኅርመተ መባልዕት
ግዝረት በስምንተኛ ቀን
ሥርዓተ ማኅሌትና መሣሪያዎቹ
ክብረ ታቦትና የበዓላት አከባበር ወዘተ
ከብሉይ ኪዳን የእምነት ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። ከዚህም ጋር በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ያላት የቦታ ይዞታ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ቀድማ የብሉይ ኪዳን እምነት ባለቤት ከሆነችው ከኢየሩሳሌም ጋር የረዥም ጊዜ የእምነትና የታሪክ ግንኙነት እንደነበራት የሚያስረዳ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስም ኢትዮጵያ በአንድ አምላክ የምታምን መሆንዋን ደጋግሞ ይናገራል። ስለዚህም ዋናዎቹ ጥቅሶች የሚከተሉት ናቸው።
«ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» (መዝ.፷፯፥፴፩)
«የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይ ደላችሁምን» (አሞጽ.፱፥፯)
«ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል» (ሶፎ.፫፥፲)
ኢትዮጵያ ከ፯፻ዥ፪፣ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እስከ ፴፬ ዓመተ ምሕረት ድረስ የብሉይ ኪዳንን እምነትና ሥርዓት ጠብቃ ኖራለች።
ክርስትና በኢትዮጵያ
እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ለሕዝቡ ያናገረው ትንቢት ሁሉ በየጊዜው ተፈጽሞአል። ገና ያልተፈጸመ ቢኖርም እንደሚፈጸም የታመነ ነው። እነሆ «ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» (መዝ፷፯፥ ፴፩) ተብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ኢትዮጵያ በ፴፬ ዓ.ም የክርስትና እምነትን ተቀበለች ይህም የሆነው በሐዋርያት ሥራ ፳፥፳፯–፴ እንደምናነበው የኢትዮጵያ ንግሥት የገርሳሞት(ሕንደኬ) ሙሉ ባለሥልጣን ቀደም ብሎ በተቀበለው የብሉይ ኪዳን እምነት መሠረት በዓለ ፋሲካን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሳለ በወንጌላዊው በፊልጶስ ትምህርት አምኖ በተጠመቀ ጊዜ ነው።
ጃንደረባው ወደ ሀገሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውንና የተረዳውን ለወገኖቹ ለኢትዮጵያውያን እንዳስተማረ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ የሚከተለውን ጽፎአል «የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሥልጣን ምሥጢረ ቃለ እግዚአብሔርን ከወንጌላዊው ከፊልጶስ ተምሮ ያመነ፣ አይሁዳውያን ካልሆኑ ወገኖች የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ ነው። ለወገኖቹም የመጀመሪያው ሰባኬ ወንጌል እርሱ ነው፣ በእርሱም አማካኝነት በመዝሙር ፷፯፥፴፩ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል» (አውሳብዩስ ፪ኛ መጽሐፍ ቁ.፩)።
ከጃንደረባው ቀጥሉም ቅዱሳን ሐዋርያት ማቴዎስ፣ ናትናኤል፣ በርተሎሜዎስና ቶማስና በኖብያም በኢትዮጵያ ቅዱስ ወንጌልን መስበካቸው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች በእነ ሩፊኖስና ሶቅራጥስ ተመስክሮአል።
የክርስትና እምነት ከሥርዓተ ጥምቀቱና ከወንጌል ትምህርቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ቢገባም ጳጳስ ባለመኖሩ ሥርዓተ ቁርባንና ሌላውም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሳይፈጸም እስከ ፫፻፴ ዓ.ም ድረስ ቆይቶአል። በ፫፻፴ ዓ.ም በትውልዱ ጢሮሳውያዊ፣ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የነበረው ቅዱስ ፍሬ ምናጦስ በንጉሡ በኢዛና ፈቃድ ወደ እስክንድርያ ተልኮ በ፳ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ በቅዱስ አትናቴዎስ ጵጵስና ተሾሞ ተመለሰ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በምልዓት መፈጸም ጀመሩ። የክርስትናው ሃይማኖት ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነ፤ ቀደም ብለው የክርስትናውን እምነትና ትምህርት በሚገባ ለተማሩትና ብቁ ለሆኑት የዲቁናና የቅስና መዓርግ ተሰጣቸው፣ ምኩራባት ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ተለወጡ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ፣ ወንጌልም በየአውራጃው ተሰበከ። ቅዱሳት መጻሕፍትም ተተረጐሙ። ቅዱስ ፍሬምናጦስ በዚህ ሁሉ ሥራው «ከሣቴ ብርሃን ሰላማ» የሚል ቅጽል ተሰጠው ከእርሱም ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች።
በ፭ኛው ምእት ዓመት (በ፬፻፯) ከሶርያና ከታናሽ እስያ ዘጠኙ ቅduሳን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ብዙ መንፈሳዊyat ተግባratin አከናው ነዋል። ከሠሯቸውም ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ:-
- ሥርዓተ ምንኩስናን፣
- ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ማስተማር፤
- በቅዱስ ፍሬምናጦስ ጊዜ ያልተተረጐሙ መጻሕፍትን መተርጐም፤
- ገዳማትን በየቦታው ማቋቋም፤
- በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ጊዜ የተቋቋመችውን ቤተ ክርስቲያን ማጠናከርና የመሳሰሉት ናቸው።
በዚህም የተቀደሰ ተግባራቸው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ተብለው ይከበራሉ። በስማቸውም ቤተ ክርስቲያን ታንጾላቸዋል።
ከዚህ በኋላ በ፮ኛው ምእት ዓመት (፭፻፬–፭፻፰ ዓ.ም) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ይህም የታላቁ ሊቅ የቅዱስ ያሬድ መነሣት ነው። ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የምትጠቀምባቸውን ጸዋትወዜማ በ፪ ዓይነት ስልተ ድምጽና እጅግ ባማረ ጣዕመ ዝማሬ ያዘጋጀ እስካሁን ተወዳዳሪ የሌለው የመንፈሳዊ ዜማ ደራሲ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት፣
«አልቦ እምቅድሜሁ
ወአልቦ እምድኅሬሁ
ማኅሌታይ ስብእ ዘከማሁ»
ከእርሱ በፊት፣ ከእርሱም በኋላ እንደ እርሱ ያለ ማኅሌታዊ (የዜማ ሰው) የለም በማለት ያደንቁታል። ቅዱስ ያሬድ ያዘጋጃቸው ፫ ዓይነት ስልተ ድምጽም ግእዝ ዕዝልና አራራይ ናቸው። ዛሬ ማንኛውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚፈጸመው ቅዱስ ያሬድ ባዘጋጀው ዜማ ነው።
ከ፲፪ኛው እስከ ፲፭ኛው ምእት ዓመት የእስልምና እምነት ተከታዮች ሰሜን አፍሪካንና እስያን በከፊል እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ በመውራራቸውና ይህም ሁኔታ እስከ ቀይ ባሕር ደርሶ ስለ ነበር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድርያና ከሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራት ግንኙነት ተቋርጦ ነበር። በ፺፱ኛው ምእት ዓመት በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ቤተ አይሁድ መካከል ዮዲት የተባለች የክርስትና ሃይማኖት ተቃዋሚት ተነሥታ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከባድ ጥፋት አድርሳለች፣ ምእመናንንና ካህናትን አስገድላለች።
ከ፲፪ኛው እስከ ፲፭ኛው ምእት ዓመት የነበረው ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በብዛት የተነሡበት፣ በዮዲት ጊዜ የፈረሱት አብያተ ክርስቲያናት የተጠገኑበትና የታደሱበት ዘመን ነበር። በዓለም ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፉት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የታነጹት በዚህ ክፍለ ዘመን ነበር። ታላቁና ሐዲሱ ሐዋርያ ጻድቁ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫና ሌሎችም ብዙ ቅዱሳን የተነሡት በዚህ ክፍለ ዘመን ነበር። ይህ ዘመን ስብከተ ወንጌል በመላ ኢትዮጵያ የተዳረሰበት ገዳማዊ ሕይወት የተጠናከረበት፣ መንፈሳዊያትመጻሕፍት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጐሙበትና በብሔራውያን ሊቃውንት ብዙ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የተደረሱበት ነበር።
ከዚህ በኋላ ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን ለቤተ ክርስቲያናችን ከባድ የፈተና ጊዜ ነበር። የውጭ ሳይሆን የውስጥ ጠላት የሆነው ግራኝ መሐመድ የክርስትና ሃይማኖትን በሚቃወም በውጭ ኃይል እየተረዳ በ፬ሺ፭፻፴፱ ዓ.ም ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ተነሥቶ በቤተ ክርስቲያናችንና በሀገራችን ህልውና ላይ እጅግ አሠቃቂ መከራ አድርሶአል። እጅግ ብዙ ካህናትንና ምእመናንን ገድሎአል። አብያተ ክርስቲያናትንና ንዋያተ ቅድሳትን ደምስሶአል። ልበ ቀረባ የሆኑ ክርስቲያኖችንም ወደ እስልምና እንዲገቡ በማስገደድ ተከታዮቹ አድርጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ ያን ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱ የጠነከረ፣ ሥነ ምግባሩ የቀና ሃይማኖቱም የጸና ስለ ነበረ በፖርቱጋሎች ኅብረት በእግዚአብሔር ኃይል ግራኝ መሐመድን ለመደምሰስ ችሏል።
ከግራኝ መሐመድ በኋላም ጀስዊት የተባሉ የካቶሊክ ሚስዮኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይለማድረግ ባደረጉት ሙከራ የብዙ ሰዎች ደም ፈስሶአል። ይልቁንም በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት (፪ሺ፭፻፲፭-፩ሺ፮፻፳፫ ዓ.ም) የካቶሊክ ሚሲዮናው በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ብጥብጥ ፈጥረው ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭና የዉስጥ ኃይላት በየጊዜው እየተነሡ ሊያዳክሙአት ቢሞክሩም የሚደርስባት መከራና ፈትና ሁሉ ኃይልዋ በሆነው በክርስቶስ ድል እያደረገች ኖራለች።
ቤተክርስቲያናችን ከ፬ኛው እስከ ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ከእስክንድርያ ተሾመው በሚመጡ ብፁዓን ጳጳሳት የበላይ መንፈሳዊ አመራር ሥር ቆይታለች። ይሁን እንጂ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ጳጳሳት ሥልጠናቸው ክህነትና ቡራኬ መስጠት ነገሥታትን እየቀቡ ማንገሥ ብቻ ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱ ማንኛውም አስተዳደር ግን እስከ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቀዳማዊ እጨጌ ድረስ በሊቃነ ካህናት ሲሆን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት በኋላ የእርሳቸው መንበር ወራስያን በሆኑት እጨጌዎች ነበር። መንበረ እጨጌውም የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ደብረ ሊባኖስ ነበር። የእጨጌዎችን ስምና የቅደም ተከተል ተራ እንደዚሁም በእጨጌነት የኖሩበትን ዘመን በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ አቅርበነዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ በቅዱስ ሐርቤ (፩ሺ፩፻፲፯-፩ሺ፩፻፶፯ ዓ.ም) ኋላም በአጼ ዮሐንስ ራብዓዊ (፪ሺ፰፻፷፫-፭ሺ፰፻፹፩) ዓ.ም ከሊቃውንት መካከል መርጣ ጳጳስ ለመሾም ለእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ደጋግማ ያቀረበችው ጥያቄ በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ላይ መልስ አግኝቶአል።
በዚህም መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ በንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ግንቦት ፳፭ ቀን ከራስዋ ሊቃውንት መካከል አራት አበውን መርጣ ካይሮ ላይ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ ዮሐንስ ፲፱ኛ አንብሮተ እድ እንዲሾሙ አድርጋለች። እንዲሁም በ፮ሺ፱፻፳፪ዓ.ም የግብጹ ፓትርያርክ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ዕጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ሳዊሮስ ጳጳስ ብለው ሾመዋቸዋል። ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ቤተ ክርስቲያንዋንም ካቶሊክ ለማድረግ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንትንም ለማጥፋት ከ፲፱፻፳፰–፲፱፻፴፫ ዓ.ም ኢጣሊያ በኢትዮ ጵያ ላይ ወረራ አደረገች። በዚህም ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሳቅርሶች ተቃጠሉ፣ ንዋያተ ቅድስት ተዘረፉ፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ዲያቆናት ምእመናንም ተገደሉ።
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን የግፍ ዘመን በትዕግሥት አሳልፋና እንደገና ተደራጅታ ለሕዝቡ አገልግሎቷን ቀጥላለች። ከጠላት ወረራ በኋላም ቀደም ሲል ከተሾሙት አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መካከል ሦስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ በአንድ ጳጳስ ብቻም ብዙ መንፈሳዊ ተግባርን ማከናወን ስለማይቻል እንደገና ሐምሌ ፲፰ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም ካይሮ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ዳግማዊ አንብሮተ እድ አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ተሾሙ። ከሊቀ ጳጳስ ቄርሎስ ግብጻዊ ሞት በኋላም ጥር ፮ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተብለው በፓትርያርክ ዮሳብ ዳግማዊ ተሠየሙ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ አኳኋን ከኃይል ወደ ኃይል ከዕድገት ወደ ተሻለ እድገት እየተራመደች ቆይታ በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም ሰኔ ፳፩ ቀን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ መጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ። እነሆ ይህ ራስን ችሎ በራስ የመተዳደር መብትና ሥልጣን ሊገኝ የቻለው በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ጥረት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ፍላጎትና በእስክንድርያውያንም ስምምነት መሆኑ ምን ጊዜም ታሪክ የማይረሳው ነው።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጻነትና ዕረፍት አግኝታ በሰላምና በኅድአት ሕዝቡን እያገለገለችና ቅዱስ ወንጌልን እየሰበከች ስትኖር እንደ ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የውስጥ ተቃዋሚ ኃይል ተነሣ ይህም «እግዚአብሔር የለም» ባዩ የደርግ መንግሥት ነበር። በዚህም ጊዜ በኢትዮጵያና በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ ብዙ ጥፋት ደርሶአል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳቱና ካህናቱ ለብዙ ዓመታት በእስር ቤት ተሠቃይተዋል። በመጨረሻም ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ቴዎፍሎስ በግፍ ተገድለዋል።
በመሆኑም ፫ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተተክተው ለ፩፪ አመታት መርተዋል። በዘመናቸውም በቤተክርስቲያን ከፍተኛ ዕድገት የታየበት፣ ሰበካ ጉባኤ የተጠናከረበት ወቅት እንደነበረ ታሪክ ለዘላለሙ ሲያስታወሰው ይኖራል። ከእሳቸው እረፍት በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተተክተው ለ፳ ዓመት ያህል ቤተክርስቲያኑን በመምራት የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደር፣ በየአብያተ ክርስቲያኑ ከፍተኛ የልማት ተቋማትን አከናውነው አልፈዋል ። በአሁኑ ጊዜ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በቀጣይም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተክተው የቤተክርስቲያኒቱን የ እለት እለት አገልግሎት እየመሩ ይገኛሉ።
«እናት ልጅዋን ትረሳለችን? ከማኅፀንዋ ለወለደችውስ አትራራምን? ምናልባት እናት ይህን ብትረሳ ጽዮን ሆይ እኔ አንችን አልረሳሽም አለ እግዚአብሔር» ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ፵፱፥፲፬ ፲፭) እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመከራው እንድትጠፋ አልተዋትም። በመከራዋም ጊዜ ሁሉ አልረሳትም። ያን ሁሉ የፈተና ጊዜ አሳልፋ ሁሉንም አስተካክላ እግዚአብሔርንም ሕዝቡንም በማገልገል ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ችላ በራስዋ ፓትርያርክ መተዳደር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ፮ ፓትርያርኮችን ሾማለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ፶፭አህጉረ ስብከት ያሏት ሲሆን በውጭ ሀገርም በኢየሩሳሌም፣ በካሪቢያን ደሴቶችና በላቲን አሜሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በካናዳና በሌሎችም አህጉረ ስብከት አሏት። የተከታዮችዋ ምእመናን ቁጥርም ከ፷፭ በመቶ በላይ ሲሆን ወደ ፸ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ፭ መቶ ሺህ ያህል ካህናት እና ከ፶ ሺህ በላይ የሰበካ ጉባኤ አብያተ ክርስቲያናት አሏት።
«ይትባረክ እግዚአብሔር ዘአልዐላ ለጽዮን እምኵሉ ዓለማት»
ቤት ክርስቲያንን ከሁሉ ይልቅ ከፍ ከፍ ያደረጋት እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትናንትና ዛሬ
አ.አ መስከረም ፲፱፻፺